የኦሮሞ እናቶችና ያልተነገረው ገድላቸው!

#ሲቄ #የሴቶች_መብት_ተሟጓች_ተቋም

በአለም አቀፍ ደረጃ የሴቶችን መብት ፣ የሴቶችን ንብረት የማፍራትና የመያዝ መብት ብሎም በፍትህ እና በአስተዳደራዊ ስርአቶች ላይ ተሳታፊ ለማድረግ ትግል ሲደረግ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም እንደ ቦረና በመሰሉ አካባቢዎች የሴቶች መብት የተረጋገጠ ነበር። ይህም በስፍራው ያሉ ኢትዮጵያውያን ንቃተ ህሊና የበለፀገ እንደነበር አንዱ ማሳያ ነው። 

ሲቄ በቦረና እና መሰል አጎራባች የኦሮሚያ አካባቢዎች የሚገኝ የሴቶችን መብት የሚያስከብር ፣ በሀይማኖት እና በፖለቲካ ከወንዶች ጋር ያላቸውን ልዩነት እና አንድነት የሚተነትን እና ለሴቶች መብት የሚሟገት ጥንታዊ ተቋም ነው። ሲቄ የሚባለው በትር እንደሆነ የሚናገሩት የኦሮሞ እናቶቻችን አንዲት ልጃገረድ ስታገባ ከእናቷ የሚሰጣት ውርስ ነው። ይህ ሲቄ የተሰኘ በትር አባገዳ ከሚይዘው በትር ጋር እኩል ዋጋ አለው። 

አንዲት ሴት በወንድ ብሎም በፍትህ ስርአቱ ጥቃትና መገለል ቢደርስባት ለሲቄ አባላት ትናገራለች። አባላቱም በትራቸውን በመያዝ በእልልታ አደባባይ ይወጣሉ። በዚህ ወቅት እልልታውን የሰማች ሴት ሁሉ ሲቄዋን ይዛ የተበደለችውን ሴት በመከተል ለፍትህ አደባባይ ይወጣሉ ሸንጎም ይቀመጣሉ። ተበዳዯ ተገቢውን ፍትህ ካላገኘች አንድም ሴት ወደቤቷ አትመለስም ። በተጨማሪ አንድ ልጃገረድ ስታገባ በሲቄ አማካይነት የኔ የምትለው ሀብት እንዲኖራት ይደረጋል። ብቻ ሲቄ ብዙ አስደናቂ የሆነ የተቋም እና ዲሞክራሲያዊ አሰራር ያለው መላው ኢትዮጵያውያን ሴቶች አብነት ሊያደርጉት የሚገባ ቀዳሚ የሴቶች መብት ጠባቂና አስጠባቂ ማህበረሰባዊ ተቋም ነው። እኔ ባጎደልኩ ታሪኩን የምታውቁ እንድትጨምሩበት ከትህትና ጋር ጠይቃለሁ። ይህን መሰል ቀዳሚ እሴቶች በማስተዋወቅ ልንጠመድ ይገባል እላለሁ። መልካም ሰንበት!

#ጥንታዊነት_የዘመኑ_ፋሽን_ነው 

#ራፋቶኤል

 

 

 

ይከተሉን!