ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ እረፍት አስመልክቶ በስርአተ ቀብራቸው ላይ የንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ንግግር: 

",, አሁን የአዳምን ልጆች ወግ ሲቀበል የምታዩት ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ በአገራችን ሥርዓት በመልካም አያያዝ ያደገ ከኢትዮጵያም ከፍ ካሉት ሊቃውንት የሚቆጠር ነው። ብልሃቱንና ትጋቱንም ለመልካም ሥራ የሚያገለግሉ መሣሪያዎች ስላደረጋቸው በመንግሥታችን ሥራ ለመመረጥና ወደ ታላቁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ለመድረስ በቃ። በየጊዜው የጻፋቸው ከፈትኛ ባህሪውን የሚገልጹ መጻሕፍት፤ ይልቁንም በቤተ ክህነትና በታሪክ እውቀት በዓለም ሊቃውንት ዘንድ የታወቀና የተከበረ አደረጉት። ለምታውቁት ሰው ከታሪኩ ከዚህ የበለጠ ልነግራችሁ የሚያስፈለግ አልመሰለኝም።

በአጭሩ ከጠባዩ ትልቅነት የሚሰማኝን ለመናገር ሳስብ ጊዜውን ሁሉ ቁም ነገር በመሥራት ማሳለፉ፤ ከራሱ ይልቅ የተቸገሩትን ለመርዳት መጣሩ፤ እውነትን፣ ፍርድንም ማክበሩና በአገር ፍቅር መቃጠሉ ትዝ ይሉኛል።

አገልጋዬና ወዳጄ ኅሩይ! በተቻለህ ስለአገርህ ሥራህን በሚገባ ፈጽመህ በምትሰናበትበት ጊዜ ታላቅ ነህ ሳልልህ ብቀር ሥራዎችህ ቀድመውኝ ይናገራሉ። በክፉ አድራጊዎች የሚገፋ የዓለምን ፀጥታ የሚያናውጥ ነፋስ ምንም ቢያንገላታህና በታላቅ ፈተና ላይ ቢጥልህም ሊያሸንፍ አልቻለም። ታላቅና ቸር በሆነው ጌታ በተመደበው ሕግ ግን መታዘዝ ግድ ሆነብህ። ይህም ለያንዳንዳችን የሚደርሰን ዕድል ነው። አንተም እስከ መጨረሻ ከታገልክ በኋላ ዛሬ ደከመህ፣ አንቀላፋህም። በሥጋ ብትለየንም ስምህና ሥራህ በመካከላችን ይኖራሉ።

ኅሩይ! እግዚአብሔር ሲያስበን አጥንቶችህና መንፈስህ የሚሰፍሩበትን ቦታ እስኪያዩና ከአባቶችህ እስኪቀላቀሉ ድረስ በእንግድነት በመጣህበት በዚህ ሥፍራ በሰላም ዕረፍ።»

ምንጭ: ዊኪፔዲያ

 

 

 

ይከተሉን!